Monday, June 4, 2018

የዶ/ር አብይ ባለቤት ቀ/እ ወይዘሮ ዝናሽ ታያቸው ለካ ….

ቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ዝናሽ ታያቸው ብሬ ዘገየ ለካ የደጃዝማች ብሬ ዘገየ የልጅ ልጅ ናቸው
ክቡር ደጃዝማች ብሬ ዘገየ የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት ብዙ የጀግንነት ገድሎችን የፈፀሙ ሰው ናቸው፡፡

ክቡር ደጃዝማች ብሬ ዘገየ በጠገዴ፣ በወልቃይት፣ በወገራ፣
በጭልጋ አውራጃዎች እና በሌሎች ቦታዎች እጅግ አኩሪና አስደናቂ ውጊያዎችን በመምራት ብዙ ጦርነቶችን በአሸናፊነት ደምድመዋል፡፡
የጣልያን ጦር የአርበኛውን የደጃዝማች ብሬን ስም ሲሰማ በፍርሀት መሸሽ የተለመደ ተግባሩ እንደነበር ይነገራል፡፡
አርበኛው ደጃዝማች ብሬ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት መቀስቀስ በኋላ የእንግሊዝ ጦር በሱዳን በኩል ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ አነሱ፡፡
‹‹ነጭን ጠልተን እየተዋጋን እንደገና ከኋላችን ሌላ ነጭ ማስገባት
ለምናደርገው ትግል አደጋ አለው›› በማለት በእንግሊዞች በሚደረገውን እንቅስቃሴ እንደማይስማሙ ተናገሩ።
ሆኖም ብዙ ውይይት ከተካሄደ በኋላ ደጀዝማች ብሬ ዘገየ እንግሊዞች ትብብር የማድረጋቸውን ሃሳብ ተቀበሉ።
የእንግሊዙ ሻለቃ በንቲክ እና ጸሐፌ ትእዛዝ ኃይሌ ወልደሩፋኤል ግን በክቡር ደጃዝማች ብሬ የመጀመሪያ አቋም ላይ ከፍተኛ ቅሬታ እንደተሰማቸው ቀረ።
አገር ነጻ ከወጣ በኋላም እነ ጸሐፌ ትእዛዝ ኃይሌ ወልደሩፍኤል፣
ክቡር ደጃዝማች ብሬ ዘገየ በትግሉ ጊዜ ‹‹ከነጭ ጋር እየተዋጋን ሌላ ነጭ አንቀበልም›› ያሉትን በማስታወስ
በሥራ ድልድል ወቅት ለደጃዝማቹ ለአርበኝነታቸው የሚመጥን የስራ
ድልድል በመንሳት ይልቁንም ከጣሊያን ጋር ወግነው ሲወጓቸው ከነበሩት ባንዳዎች በታች መድበዋቸው ነበር፡፡
መላው አርበኛም በነጸሐፌ ትእዛዝ ኃይሌ ወልደሩፋኤል ድርጊት በጣም ቅሬታ ተሰማው።
ክቡር ደጃዝማች ብሬ ግን ‹‹እኔ የተዋጋሁት ለአገሬ እንጂ ለነኃይሌ ወልደሩፋኤል አይደለም፤ ለጃንሆይም ስልጣን አነሰኝ ብየ
ቅሬታ አላቀርብም!›› በማለት ቅር እንደማይላቸውና ወገንተኝነታቸው ለአገራቸው እንጂ ለስልጣን እንዳልሆነ በግልፅ ተናገሩ፡፡
ክቡር ደጃዝማች ብሬ ዘገየ በተለያዩ ጊዜያት የላይ አርማጭሆ ምስለኔ፣
የጎንደር አውራጃ ነጭ ለባሽ ጦር አዛዥ፣ የአርማጭሆ ወረዳ ገዥ
እንዲሁም የስሜንና በጌ ምድር ጠቅላይ ግዛት ነጭ ለባሽ ጦር ዋና አዛዥ ሆነው አገራቸውን በቅንነት አገልግለዋል።
በመጨረሻም ክቡር ደጃዝማች ብሬ ዘገየ በ1959 ዓ. ም. ከንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘንድ ተጠርተው ከልዩ ልዩ
ሽልማቶች ጋር አንድ ላንድሮቨር መኪና ተሸልመው ወደ ጎንደር
ሲመለሱ በደረሰባቸው የመኪና አደጋ በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በዚሁ ዓመት (በ1959) ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።
ምንጭ፡ የጎንደር ኅብረት የፌስቡክ ገጽ

No comments:

Post a Comment