Friday, July 27, 2018

‹‹በኢንጂነሩ መሞት ተዳፍኖ የሚቀር ሚስጥርም ሆነ ግድብ ሊኖር አይችልም›› (አሳዬ ደርቤ)

ከቀናት በፊት የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር አቢይ አቢይ አህመድ ሙህራንን ሰብስበው በነበረበት ወቅት ‹‹በእስካሁኑ ፍጥነታችን የምንቀጥል ከሆነ የአባይ ግድብ የዛሬ አስር ዓመትም አያልቅም›› ብለው በተናገሩ ማግስት፤ የአባይ ግድብ ስራ አስኪያጅ የሆኑት ‹ኢንጂነር ስመኛው በቀለ› መስቀል አደባባይ ላይ በጥይት ተመትተው መሞታቸውን ሰማን፡፡


እንግዲህ ኢንጂነር ስመኘውን የገደሉት ‹ሚስጥር ያወጣብናል› ብለው የፈሩ ሰዎችም ይሁኑ ‹የግድቡን መቋረጥ የሚፈልጉ ሐይሎች› ለአሁኑ ግልጽ ባይሆንም የሞተበት መንገድ ግን ያሳዝናል፡፡

ይሄን ያህል ግዙፍ ፕሮጀክት የሚመራ መሃንድስ ያለምንም ጠባቂ ብቻውን ሲንቀሳቀስ መገደሉም የመንግስትን እንዝላልነት ያሳያል፡፡ ሌቦች ባለስልጣናት በስንት ጋርድ ተከበው በሚሄዱባት አገር ላይ የስንት አገራት ትኩረት ያረፈበትን ግድብ በስራ-አስኪያጅነት የሚመራ ኢንጂነር ጎን… አንድ እንኳን የታጠቀ ሃይል አለመኖሩ ያሳዝናል፡፡
ይሄም ሆኖ ግን አባይ በረሐ ውስጥ ቀን ከሌት ሲንከራተት…. ግድቡን ሊጎበኙ የሚሄዱትን ሰዎች ሁሉ እየተቀበለ ያለምንም መሰላቸት ማብራሪያ ሲሰጥ የኖረ ሰው የልፋቱን ፍሬ ሳያዬው በአጭር መቅረቱ አንጀት ይበላል፡፡ ግድቡ በተመረቀ ማግስት እኛን ሊሰበስብበት የሚገባው ቦታ ላይ በነፍሰ-በላዎች ጥይት ደሙ ተንዠቅዥቆ መገኘቱም በሃዘን ያንገበግባል፡፡

በሌላ መልኩ ግን ለእኛ ለኢትዮጵያኖች የኢንጂነሩ መሞት ብርታታችን እንጂ ሽንፈታችን ሊሆን እንደማይችል የገደሉት ሐይሎች ማወቅ ይኖርባቸዋል፡፡ አዎ! በጥይት የተገደለው ስራ አስኪያጁ እንጂ ስራው አይደለም፡፡ እሱ ቢሞትም የእሱን ስራ ማስጨረስ የሚችሉ መሃንዲሶች አገራችን አታጣም፡፡
ሲቀጥል ደግሞ ኢንጅነሩ የተገደለው ‹ሚስጥር ያወጣብናል› ተብሎም ሆነ ‹የግድቡን ግንባታ ያስተጓጉላል›………. ሁለቱም ሃሳባቸው አይሳካም፡፡ በኢንጂነሩ መሞት ተዳፍኖ የሚቀር ግድብም ሆነ ሚስጥር ሊኖር አይችልም፡፡

እኛም እየተቀዛቀዘ ያለውን የግድብ ግንባታ በአዲስ ሐይል ተነሳስተን እንጨርሰዋለን፡፡ ኢንጅነሩ የደከመለትንና የሞተለትን ፕሮጀክት ቀን ከሌት በመስራት ህልሙን እውን እንደርገዋለን፡፡
ይሄም ብቻም አይደለ! ግድቡንም በስሙ እንሰይምለታለን፡፡
.
መንግስታችን ግን እንደ ኮሎምበስ ከአገር አገር መዞሩን ትቶ አገራችን ላይ ሰላምንና መረጋጋትን ቢያሰፍን ጥሩ ይመስለኛል፡፡ ከመቼውም ጊዜ በላይ ሐገራችን ውስጥ ህገ-ወጥነትና አድሃሪነት እየሰፈነ ቢሆንም… መንግስት ዙረቱን ቀነስ አድርጎ ህግን የማስከበር ስራን መስራት አልቻለም፡፡
ከትናንት ወድያ……. የዳንጎቴ ሲሚንቶ ስራ አስኪያጅ በጥይት ተቦዳድሰው ተገኙ፡፡
ትናንት……… ጠቅላይ ሚኒስቴሩ አጠገብ ቦንብ ፈነዳ፡፡
ዛሬ ደግሞ…….. የአባይ ግድብ ስራ-አስኪያጅ ጠቅላይ-ሚኒስቴሩ በተሳቱበት ቦታ ላይ ግንባራቸውን በጥይት ተመትተው ተገኙ፡፡
ይሄም ሆኖ ግን በየቀኑ የምንሰማው ስለ ሟች እንጂ ስለ ገዳይ አይደለም፡፡ የገዳዮቹን ማንነት መንግስታችን ቀርቶ FBIም ሊደርስባቸው አልቻለም፡፡
አሁን ግን በዚህ ሁኔታ መቀጠል የለብንም፡፡ መንግስት ዙረቱን ትቶ የዜጎቹን ደህንነት በቃልም ሆነ በሃይል ሊጠብቅና ሊስጠብቅ ግድ ይለዋል፡፡ የኢንጂነሩንም ገዳዮች አጣርቶ በአስቸኳይ ለፍርድ ሊያቀርብልን ይገባል፡፡
በመጨረሻም አምላክ የኢንጂነሩን ነፍስ በአጸደ-ገነት እንዲያስቀምጥልን እመኛለሁ፡፡

No comments:

Post a Comment